ሁሉም ባለድርሻ አካላት የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከል መረባረብ አለበት!
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አጉኔ አሾሌ እንዳሉት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ የመከላከያ ሥራዎች በየደረጃው ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው አካባቢዎችና በተመረጡ ወረዳዎች ላይ እየተካሄደ ያለው ቤት ለቤት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ እንደሚገባ አቶ አጉኔ አሳስበዋል።
ሁሉም መዋቅሮች የተለቀቀውን በጀት በተለይም የGAVI በጀት የተጠቃለለ ሂሳብ ሪፖርት እስከ ነገ መላክ እንዳለባቸውም በመጠቆም።
የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ምንተስኖት መልካ በበኩላቸው የወባ መከላከልና ቁጥጥር ጥረቶች ሁሉም መዋቅሮች ሁሉን አቀፍ የመከላከልና የቁጥጥር ስልቶችን መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የተሰማሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት የምላሽ ሥራዎችን እስከ ቤተሰብ ደረጃ ድረስ በመድረስ መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለጤና አገልግሎቶች ማስፈጸሚያ የተላኩ ገንዘብ በዋናነት የGAVI በጀት በአገባቡ ተጠቅመው ሪፖርት እንዲያደርጉ በድጋሜ ተጠይቋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጮሌ ሹምቡሎ የዞኖችና የሪጅዮፖሊስ የGAVI በጀት አጠቃቀም ያለበት ደረጃ ሪፖርት በማቅረብ የበጀት ሪፖርት ያላጠናቀቁ መዋቅሮች ላይ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
በበይኔ መረብ ውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ለወባ በሽታ መከላከል ማህበረሰቡን በማሳተፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ማጠናከር፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል።




