“ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ የክልሉ የጤና ሽፋን 90 ከመቶ ማድረስ ተችሏል!”

እንዳሻው ሽብሩ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ
‎
‎በጤናው ዘርፍ ሪፎርም፣ በሁለተኛው መካከለኛው ዘመን የጤና የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድና ጤና ተግባቦት ዙሪያ ክልል አቀፍ ስልጠናና ውይይት ተጀምሯል።
በክልሉ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ጤና ቢሮ ኃላፊ አስታወቁ።
‎
‎በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ እንዳሻው ሽብሩ፤ የጤናው ሴክተር ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያተከናወነ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የሰው ሀብት ብቃት፣ የባለሙያ ቁጥር፣ ስርጭት፣ ተነሳሽነት፣ የመረጃ ጥራትና አመራር ውጤታማነትን የሚወስኑ መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ቢሮ ኃላፊ እንዳሻው ተናግረዋል።
‎
‎ሪፎርሙ በንድፈ ሀሳብ ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን ሥር ነቀል ስኬቶችንና ፋይዳዎችን እያመጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በሆስፒታሎችና በሌሎች በጤና ተቋማት የአገልግሎቶችን ተደራሽ፣ ፈጣንና እርካታ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል ።
‎
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊው እንዳሻው በንግግራቸው፤ የክልሉ የጤና ሽፋን 90 ከመቶ መድረሱን ገልፀው፤ ፈጣን ፣ ቀልጣፋና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
‎
‎ሪፎርሙ የመድሃኒት የህክምና መገልገያ ግብዓቶች አቅርቦት ሰንሰለትን በማሻሻል የተቋማት ንብረት ብክነትን የቀነሰ ከመሆኑም ባሻገር በክልሉ 83 ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት መደብሮች ለህዝብ መከፈታቸውንም ጠቁመዋል።
‎በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የሚኒስቴር ዴኤታ ጽ/ቤት አማካሪ ‎ዶክተር ደሳለኝ በቀለ፤ በሀገራችን ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲፈጠር የጤና ሪፎርም ትግበራ ላይ ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
‎የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ፤በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ የኢንቨስትመንት እና የሪፎርም ተግባራት ዙሪያ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
‎በጤና ሴክተር ሪፎርም እና በሁለተኛው የጤና ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ዙሪያ ሀገር አቀፍ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።