ወቅታዊ የአየር ንብረት ለዉጥ መረጃዎችን ለዉሳኔ መጠቀም ተፈጥሯዊ እና በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ የሚችሉ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመለየት፣ ለማንቃት እና ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑ ተገለፀ፡፡

 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር 13ኛ ሳምንት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል ግምገማ ማካሄዱን አስታዉቋል፡፡
በዉይይት መድረኩ በትኩረት ከታዩ ጉዳዮች የስርዓተ-ምግብ እጥረት ልየታና ህክምና ፤የወባ በሽታ ስርጭት በተለይም በከተሞች ላይ እየጨመረ ያለዉን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀነስ መወሰድ ያለበት መከላከልና የቁጥጥር ተግባራት፣ ክትባት ባለማስከተብ የሚከሰቱ በሽታዎች ቅኝትና አሰሳ፣ የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት እና ሌሎች በሽታዎች በዝርዝር የተገመገመ ስሆን ተግዳሮቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ተመላክቶበታል፡፡
በሳምንቱ ልዩ ትኩረት የተሰጠዉ የወባ በሽታ ስርጭት በከተሞች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከመሆኑ አኳያ፣ ማህብረሰቡን በማነቃነቅ፣ መጠነ ሰፊ የመከላከል እና መቆጣጠር ተግባራት ማከናወን እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
በተጠናከረ የምላሽ ሥራ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ መቆጣጠር የተቻለ ስሆን፣ ቀጣይ እንደ ሀገር በዘመቻ ለሚሰራዉ ማጠናከሪያ ክትባት በየደረጃዉ ቅድሜ ዝግጅት ሥራ ተጠናክሮ መሰራት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ በተጨማርም የአንደኛ ዙሪ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ብልቃጥ ወደ ኃላ አመላለስ ላይ ያለዉ መረጃ የተገመገመ ስሆን፤ በወረዳዎች ደረጃ አማላለስ ላይ ችግሮች መኖራቸዉ ተገምግሟል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተር አቶ ምንተስኖት መልካ ባስተላለፉት መልዕክት የአንደኛ ዙሪ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ብልቃጥ አመላለስ ላይ ያለዉ ችግር በፍጥነት መፈታት እንዳለበት አንስተዋል፡፡
በተጨማርም የሥርዓተ-ምግብ እጥረት ችግርን ለመፍታት ቀጣይነት ያለዉ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና የወባ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች መጠናከረ እንዳለበት አንስተዉ፣ ቀጣይ ወቅቱን ባገናዘበ ሁኔታ የአከባቢ ቁጥጥር ተግባራት መከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ም/ዳይሬክተር አቶ ምንተስኖት መልካ አክለዉም ወቅታዊ የአየር ሁኔታ መረጃዎችን ለዉሳኔ መጠቀም የመሬት መንሸራተት፣ጎርፍና ሌሎች ተፈጥሯዊ እና በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ የሚችሉ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመለየት፣ ለማንቃት እና ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑን ገልጹዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት::